Friday, 20 January 2017

ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች



                          ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች


ዩኒቨርስቲዎች ለአንዳንዶች አዲስ ፍቅር የሚጠነሰስባቸው አምባዎች፣ ለሌሎች የትዳር ማኮብኮብያ ሜዳዎች ናቸው፡፡ በዩኒቨርስቲ ግቢ ማጥናትም መጠናናትም ያለ - የነበረ - የሚኖር ጉዳይ ነው ፡፡ በዩኒቨርስቲዎቻችን ዙርያ ስለሚጣዱ ‹‹ ሁለት ጉልቻዎች ›› ለማስቃኘት የገዛ ጓደኛዬን ሕይወት መመርመር   አስፈልጎኛል፡፡

ፌቨን ጓደኛዬ ናት፡፡ ተወልዳ ያደገችው ሐረር ነው። አንደበቷ የድሬ ‹‹ሐላዋ››ን ያስንቃል፡፡ ስታወራ ዉላ ብታድር አትሰለችም፡፡ የሚያዳምጣትን ሁሉ በወሬ ፉርጎ ይዛ እብስ ትላለች፡፡ ‹‹አቦ››፣ ‹‹አብሽር››፣ ‹‹ሀዬ›› የሚሉት ቃላት የወሬ ፌርማታዎቿ ናቸው፡፡ እሷ ስትላቸው እንዴት እንደሚጣፍጡ፡፡ አንዳንድ ሴት ወጥ ይጣፍጥላታል፣ ፌቨን ደግሞ ወሬ ይጣፍጥላታል፡፡

እንደ ብዙዎቹ የድሬና ሐረር ልጆች ቀጥተኛ፣ ቀልጣፋና ደፋር ናት። ድፍረቷ ግን ትንሽ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ አግብታለች፡፡ አሁን ይሄን ማን ያምናል፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ፌቨን ሙሉ ትዳር ባይሆንም ረቀቅ-ደቀቅ፣ እጥር ምጥን ያለች ጋብቻን ፈጽማለች፡፡ እኛ ከአፓርታይድ በላይ የምንፈራውን ትዳር እሷ ድንገት ስትፈናጠጥበት ማመን አልቻልንም፡፡ 

ፈጣንና ደፋር ናት ብያችሁ የለ! ትዳር ለመመሥረት የፈጀባት ጊዜ ታዲያ ሁለት ወር ብቻ ነው። አንደኛ ዓመት ተማሪ እያለች ከተዋወቀችው፣ ስሙ አብርሃም ከሚባል፣ ገና ሮጦ ያልጠገበ ከሚመስል ልጅ ጋር በተዋወቁ ልክ በሁለተኛ ወራቸው ትዳር መሠረቱ። ፌቨን ስለሁኔታው ስትጠየቅ ‹‹አታካብዱ አቦ! የምር ትዳር-ትዳር መሰላቹ እንዴ!›› ትላለች፡፡ እሷ እንዲህ የምታቃለውን ትዳር እኔ ይመጥነዋል ያልኩትን የዳቦ ስም ሰጥቼዋለሁ፤ ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር፡፡

ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር የሥርወ ቃሉ አመጣጥ ‹‹ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ›› ከሚለው ሐረግ የሚመዘዝ ሲሆን ሁለት በትኩስ ፍቅር እየከነፉ ያሉ ጥንድ ተማሪዎች ዶርም በቃኝ ብለው የክብሪት ሳጥን በምታክል ቤት ውስጥ ‹‹እኔ እብስ-እኔ እብስ›› እየተባባሉ የሚኖሩት፣ ትዳር የሚመስል ግን ደግሞ ትዳር ያልሆነ የጥምረት ኑሮ ነው። ሐረጉን የፈታው የኔ መዝገበ ቃላት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

ፌቨን የአካውንቲንግ 3ተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ አቶ “ባል” ወይም ‹‹ልጅ አብርሃም›› ደግሞ የ4ተኛ ዓመት የማርኬቲንግ ተማሪ ነው፡፡ “አራት ዓመት ከቆየሀ አይቀር ለምን አንድ ዓመት ጨምረህ ማርኬቲንግ ኢንጂነሪንግ ድግሪ አትወስድም” እያሉ የሚመክሩት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል። አያያዙን ላየው እሱም ምክሩን ተቀብሎ ቀን ከሌት ለሁለት ድግሪ የሚተጋ ነው የሚመስለው። ፌቨንና ‹‹ልጅ አብርሀም›› የተዋወቁት እሷ አንደኛ ዓመት፣ እሱ ደሞ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ኾነው ነው፡፡ ነገር ግን ከፍቅራቸው ብዛት ትቼሽ አልመረቅም ብሎ በፅናት እየጠበቃት ያለ ነው የሚመስለው።

የነ ፌቨን ቪላ

የነፌቨን “ቪላ” ስፋቷ የአንድ ደህና ሻወር ቤት ጃኩዚ ብታክል ነው። ቤቷ ከመጥበቧ የተነሳ አራቱን የአካባቢ ሳይንስ አቅጣጫዎች ያልተማረ ሰው በእንግድነት ቤታቸው ቢገባ ሊጠፋ ይችላል፡፡ የክፍሏ ደቡባዊ አቅጣጫ- ኩሽና፣ ሰሜኑ- እቃ ቤት፣ ምሥራቁ- ሳሎን፣ ምዕራቡ መኝታ ተብሎ ይጠራል፡፡ ታዲያ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ለማቋረጥ (ከጓዳ ወደ መኝታ ቤት ለመግባት) ሲያስፈልግ ሰፊ የጨርቅ መጋረጃ አንኳኩቶ ማስከፈት ግድ ነው። ጨርቅ በር አንኳኩቶ የሚያውቅ ከናንተ መሐል ምንኛ የተባረከ ነው! ‹‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል›› የተባለው የጨርቅ በር ሳይሆን አይቀርም ስል አሰብኩ፡፡

ደግሞም ሳስበው…የነ ፌቨን ቤት በዓለም ላይ መኝታ ቤት ተኝቶ በእግር ድስት መክፈት የሚቻልበት ብቸኛው ቤት ይመስለኛል። በአንድ ጥግ በኩል አንድ ከደስታ ወረቀት የሳሳች ፍራሽ ተነጥፋለች፡፡ ይቺ ፍራሽ በዳበሳ ካልሆነ አትገኝም፡፡ ብዙ እንግዶች ፍራሽዋ የወለል ንጣፍ እየመሰለቻቸው ሳይረግጧት የቀሩ አይመስለኝም፡፡ ከፍራሽዋ ጎን ደግሞ ሁለት እንደ ቁም ሳጥን የሚያገግሉ ፌስታሎች ተቀምጠዋል።

አንዱ የቆሸሹ ልብሶች የሚቀመጡበት ነው፡፡ ሌላው የታጠቡ የክት ልብሶች ይንፈላሰሱተበታል፡፡ ‹‹የቤቱ ጓዳ በሁለት ስንዝር ከመኝታ ቤቱ ሰፋ ያለ ነው›› ይላሉ እነ ቬቨን ቤት የሚመላለሱ ቤተኞች። ባለ ሁለት በር የምድር ኪችን ካቢኔት የሚመስል ነገር ባንዱ ጥግ ተቀምጧል። ከላይ የተብራራው የነፌቨን ቤት ድባብ በጥቅሉ በዩኒቨርስቲ ሕይወት የሚመሠረቱ ጥቃ ቅንና አነስተኛ ትዳሮችን ይወክላል ።



የነ ፌቨን ሕይወት ‹‹ደረጃ ሦስት›› የሚባለውን የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር የሚወክል ሲሆን ከዚህ ሻል ያሉ ‹‹ደረጃ ሁለት›› እና ‹‹ደረጃ አንድ›› ትዳሮችም አልፎ አልፎ በዩኒቨርስቲዎቻችን ዙርያ ይገኛሉ፡፡ ደረጃ ሁለት ትዳሮች ብዙዉን ጊዜ ባለ ሁለት ክፍልን የሚጎናጸፉ ሲሆን በመጋረጃ ፋንታ ግድግዳ ይለያቸዋል፡፡ ከጓዳ ወደ መኝታ ቤት ሲኬድም የምናብ ሳይሆን የጣውላ በር መክፈት ግድ ይላል። የ‹‹ደረጃ አንድ›› ትዳሮች ደግሞ የመኝታ ቤት አልጋ ያላቸው ናቸው፡፡ አልጋው ላይ የሚዘረጋው ሞልፋጣ ፍራሽ የነፌቨንን ዓይነት አምስት ጥቃቅን ፍራሽ አይወጣውም ብላችሁ ነው!
‹‹ደረጃ አንድ›› ትዳሮች የዋዛ አይደሉም፡፡ ከአዲስ ተቀጣሪ መምህር የተሻለ የቁስ ሙሌት ይታይባቸዋል፡፡ ሙቅ ሻወርና ሞቅ ያለ ገቢም አያጣቸውም፡፡ የትዳር ተጣማሪዎችም መጠኑ ከፍ ያለ ገንዘብ የሚላክላቸውና ከ‹‹ደህና›› ቤተሰብ የተገኙ ስለሚሆኑ አነስተኛ ፍሪጅና 14 ኢንች ቴሌቪዥን በቤት ዉስጥ የመገኘት እድሉ ሰፊ ነው፡፡
ወደነፌቨን የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች ስንመለስ….ሕይወት አልጋ በአልጋ እንዳልሆነች እንረዳለን፡፡

እንደፌቨን ተንደርድሮ ለመግባት ድፍረትና የወጣትነት ስሜት ብቻ ሳይሆን ሰፋ ያለ የገንዘብ ማግኛ መረብ መዘርጋትም ያስፈልጋል። የፌቨንን በመሠሉ ‹‹ደረጃ ሦስት›› ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች ቤት ውስጥ ተለይቶ የሚታይ ሳሎን የለም፡፡ ቴሌቪዥን የቅንጦት ቅንጦት ነው፡፡ ቢኖርስ የት ይቀመጣል? ፍራሽ ላይ? የተከደነ ባልዲ ላይ? 

በነፌቨን ቤት ፍራሽ የሚነጠፈው ከእኩለ ቀን በኋላ ነው፡፡ በጠዋት ፍራሻቸውን አንጥፈው ክላስ የሚገቡ ልጆች በባትሪ (ብዙውን ጊዜ መብራት ስለሚጠፋም ጭምር) ተፈልገው አይገኙም። አብዛኛውን ጊዜ ፍራሽ የማንጠፍ ኃላፊነት ደግሞ በሴቷ ላይ ይወድቃል፡፡ ነገር ግን ሁሌም ሴቷ ብቻ አታነጥፍም፡፡ ወንዱም ክላስ ከሌለው ወይም ደግሞ ከሷ ቀድሞ ቤት ከገባ ፍራሽ አንጥፎ ይጠብቃታል፡፡ በዛውም ባለሞያነቱን ያስመሰክራል። እንዲህ ዓይነቱ ወንድ ግን ከመቶ አንድ ቢገኝ ነው፡፡

በሁሉም የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች ውስጥ የቤትና የእቃ እንጂ የአኗኗር ልዩነት አይታይም። ሁለቱም በአማካይ ለአንድ ወጥ እሩብ ኪሎ ሽንኩርት፣ እሩብ ሊትር ዘይትና ሦስት ማንኪያ በርበሬ ይጠቀማሉ፤(ስለሚያቃጥላቸው ይሆን?)

 ቁርስ ላይ የፍርፍር አይነቶች ይዘወተራሉ። ምሳና ራት ላይ ደግሞ ፓስታ፣ መኮረኒ ,ድንች ወጥ፣ ሽሮ ወጥ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በነ ቬቨን ጣሪያ አልፎ አልፎ መና ይወርዳል፡፡ ያን ጊዜ ጠባቧ ቤት ቄራ ትሆናለች፡፡ ይሄ አጋጣሚ እንደ አውዳመት ስለሚቆጠር ጥቂት የክላስ ጓደኞችን ምሳና እራት መጋበዝ- ብሉልኝ ጠጡልኝ ማለት የተለመደ ነው።

የካፌ ተጠቃሚ ባለመሆን የምትከፈል ካሳ የደረሰች ሰሞን የነፌቨን ቤት ከትከት ብላ ትስቃለች፡፡ ቁርስ ስጋ ፍርፍር፣ ምሳ ጥብስ፣ እራት ጎረድጎረድ…። በዚህ ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች ዉስጥ ፍቅር ይደረጃል፡፡ ፌቨን ጥቂት ጓደኞቿን ይዛ በቤቷ ምሥራቃዊ ጥግ (ማድቤት) ጉድ ጉድ ትላለች፡፡ ከጓዳ ሆና ደግሞ ዝም አትልም፣ ‹‹አቦ አትነጅሱና! ሃዬ…አብስለን እንብላበት! ሃዬ…››የምትል ይመስለኛል…ፌቨን፡፡

እንደ ሙሉ ትዳር ሁሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር መሐል ንፋስ ይገባል፤ ፍቅር ይላላል፤ በአንድም ሆነ በሌላ አጋጣሚ፡፡  ክፍተት የሚፈጠሩበት ምክንያት ደግሞ አስገራሚ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍራሹን ማን ያንጥፈው በሚል ተልካሻ ምክንያት ጥቃቅን ትዳር ሊፈርስ ይችላል፡፡ በአነስተኛ ትዳር ዉስጥ ‹‹ካልሲህን እጠብ አላጥብም›› በቂ የፍቺ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ የሥነ ጾታ ክበባት (Gender Clubs) የሠሩትን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻና ንቅናቄን ተከትሎ ይመስለኛል የሴቶች እኩልነት በጓዳ ዉስጥም መረጋገጥ ችሏል፡፡ ከፊል ሚስት ለመሆን የበቁ ተማሪ ሴቶች ወንዱ የቤት ዉስጥ ኃላፊነቶችን በእኩል እንዲጋራ የሚሹበት ጊዜ አለ፡፡ ይህን ተከትሎ አብዛኞቹ የጥቃቅን ትዳሮች ውስጥ ምግብ በፕሮግራም መሠራት ተጀምሯል።

ሁሉም ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር በዚህ መርህ ይመራል ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህን የእኩልነት ሥርዓት በመቃወም ትዳራቸውን ፈተው ዶርማቸው የገቡ ወንዶች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ትዳራቸውን ያላፈረሱት ወንዶችም ቢሆን በዚህ ጥብቅ የእኩልነት ፍልስፍና ምክንያት ሰላማቸው መናጋት መጀመሩን አይሸሽጉም።

ይህ የእኩልነት ጥብቅ ሥርዓት በአመዛኙ ‹‹በጥቃቅን ባሎች›› ዘንድ ቅቡልነት አላገኘም፡፡ እነዚህ ‹‹ወንድ ጓዳ መልከስከስ የለበትም›› የሚል ጥብቅ አቋም የሚያራምዱ አክራሪ ወንዶችን እነፌቨን “ቦኩ ሀራም” በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸዋል። ልጅ አብረሃም አንዱ ነው፡፡ የነፌቨን ትዳር  ሸብረክ የሚለው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ‹‹አብረሃም አልፎ አልፎ ቦኮ ሀራምነት ያጠቃዋል›› ትላለች ክብርት ባለቤቱ ፌቨን ፡፡

‹‹ፈተና አለብኝ››፣ ‹‹አሳይመንት ተከመረብኝ››፣ ‹‹የቴንሽን አጋንንት ሰፈሩብኝ›› ወ.ዘ.ተ. በሚሉ ተልከሻ ምክንያቶች የቤት ግዴታውን ሳይወጣ የሚቀርበት ጊዜ አለ፡፡  “አብረን ለምንበላው እኔ ብቻዬን ምን በወጣኝ!…ሃዬ!?” እያለች ንዝንዝ ትላለች፡፡ አኩራፊ አለመሆኗ በጀ፡፡ 

ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር ለመመስረትም ሆነ ለመፋታት ብዙ ቢሮክራሲ የማይፈልግ የትዳር ዓይነት ነው። ሠርጉ ምናባዊ በመሆኑ ሲመሠረት ‹‹እወቁልኝ›› ካርድ መበተን የለ፣ ቬሎ የለ፣ መልስ የለ፣ ቅልቅል የለ፣ እንሾሽላ የለ፣ የዳቦ ስም ማውጣት የለ፣ ምን የለ…ምን የለ….፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር በአንዳች ቅንጣት አጋጣሚ ሊመሠረት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ‹‹ኦቨር›› የተመቻቹ ጥንዶች ቢደጋግሙት ነገሩ ወደ ደቃቃ ትዳር ለመለወጥ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ “የኔ ውድ! በየጊዜው ስንገናኝ የአልጋ ኪራይ ከምናወጣ ለምን የራሳችን የሆነ ቤት አይኖረንም” በሚል በርከክ ብሎ በስካር መንፈስ የጋብቻ ጥያቄ ሊቀርብና በዚያው ትዳር ሊመሠረት ይችላል፡፡

ልጅትም ነገሩ ጥሩ ሀሳብ ከመሰላት ‹‹ባንዳፍ›› ብላ የሚከራይ ደሳሳ ጎጆ ፈልጋ አፈላልጋ መጠቃለል ነው። ተማሪውም ‹‹ጠቀለላት እኮ!››፣ ‹‹ጠቀለለችው እንዴ?›› ፣ ‹‹ተጠቃለሉ ማለት ነው?›› እየተባባለ የትዳራቸውን የመሰረት ድንጋይ ይጥላል፡፡ በሂደትም ለትዳራቸውም ሙሉ እውቅና ይሰጣል።

ሰዓቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም ትዳሮች ውስጥ ሰዓት እላፊ አለ። ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ለነፌቨን የEBC  ዜና ማጠቃለያ ሰዓት ብቻ አይደለም፤ እንደ ሰዓት እላፊም ይጠቀሙበታል። አብርሃምም ሆነ ፌቨን የትም ያምሹ የት ከአራት ሰዓት በፊት ቤት መግባት ሳይጽፉት የሚተገብሩት ሕግ ነው። በሰዓቱ ቤት መግባት ያልቻለ ካለም ሲመጣ ከአሳማኝ ምክንያት ጋር መምጣት ይኖርበታል፡፡

አለበለዚያ ደግሞ ለንትርኩ እራስን በሚገባ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በአብዛኛው አጥፊው አብርሀም ነው፡፡ ማርፈዱን ተከትሎ ፌቨን ትበሳጫለች፡፡ በሐረርኛ የቡራኬ የሚመስሉ ልቅ ቃላት  ትሰድበዋለች፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ንዝንዙና ድብርቱ ትዳራቸውን ያሻክረዋል፡፡ ያን ሰሞን ፌቨን ሀያ ምናምን ዓመት ባልረባ ትዳር ውስጥ ያሣለፈች ባልቴት መስላ ቁጭ ። 

‹‹አልፎ አልፎ ከሆነኮ አምሽቶ ቢመጣም ጣጣ የለውም›› ትላለች ፌቨን፡፡ ችግሩ ከሴቶች ጋር እንዳመሸ ከጠረጠረች ነው፡፡  ቅናት ጨጓራዋን መልጦ ራቁቷን እንደሚያስቀራት ትናገራለች፡፡  ያኔ ፌቨን ስድብ የልቧን አያደርስላትም፡፡ ኩርፊያዋን ልክ እንደ ሸማ ላታወልቀው ትከናነበዋለች። አብርሀም የኩርፊያዋን ሸማ ለመግፈፍ እድሎች አሉት፡፡ ለምሳሌ በተከታታይ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እየሰራ ፌቨንን ማጉረስ።

በአንድ ወቅት በዚሁ ቅናት ምክንያት የትዳር ገመዳቸው ላልቶ ሊበጠስ ደርሶ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ትዳሯን ጣጥላ ጓደኞቿ ዶርም አንድ ሳምንት ኖረች፡፡ ታዲያ ፍቅርና ናፍቆት አንድ ላይ ተደማምረው ያቺን ተጫዋች ልጅ ክስም አደረጓት። አቤት ያኔ ላስተዋላት!! ከጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር የተፈታች የዩንቨርስቲ ተማሪ ሳትሆን ባሏ የሞተባት ወይዘሮ ነበር የምትመስለው። የኋላ ኋላ በጓደኞቿ ሸምጋይነትና በአብርሀም ይቅርታ ጠያቂነት ወደ ሞቀ ቤቷ ተመለሰች።

በጥቃቅን ባለትዳሮች ቤት ደምቆ የሚከበረው ገና ወይም ፋሲካ አይደለም፤ የልደትና የ‹‹አኒቨርሰሪ›› ፕሮግራም እንጂ፡፡ በተለይ ደግሞ ለሴቷ ልደት የተለየ ትኩረት ይሰጣል። ኬክ ይቆረሳል፣ ፓርቲ ይቀወጣል፣ ስጦታ ይሰጣጣሉ…ወዘተ፡፡ እንደዚ ዓይነት ፕሮግራሞችን ከመጠጥ እና ከጭፈራው በላይ የሚያደምቋቸው ከታዳሚዎቹ ለባለትዳሮች የሚሰነዘሩ ድንገተኛ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ጥንዶቹ ለሚጠየቁት ማንኛውም ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለባቸው ።

ለምሳሌ ፡- የት ተገናኛቹ? ምኗን ነው የምትወድላት? ምኑን ነው የምትወጂለት? First kiss መቼና የት ነበር? መጀመሪያ ቀን ሲስምሸ ምን ተሰማሸ? ለወደፊት ምንድነው እቅዳቹ? ትጋባላችሁ? ስንት ልጆችን ለመውለድ ነው የምታስቡት? የመጀመርያ ልጃችሁ ስም ማን ይሆናል? ከሌላ ሴት ጋር ተኝቶ ብታገኚው ምን ታደርጊዋለሽ? አንተስ ምን ይሰማሃል? 

አነስተኛና ጥቃቅን ትዳሮች ሲመሰረቱ ዝም ብሎ አንድ ቤት ከመጋራት ባለፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ፌቨን ትናገራለች፡፡ ያለገደብ ለመዝናናትና ባሻቸው ሰዓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፍቅር መስራት ከፋይዳዎቹ ይጠቀሳል። ከኦቨር መልስ ለአልጋ ኪራይ የሚወጣውን ገንዘብ ማስቀረት ሌላው ጥቅም ነው፡፡

አርብና ቅዳሜ ያቺ ስስ ፍራሽ እስከ ስድስት ሰው ድረስ ልታስተናግድ ትችላለች። ምግብ እንደፍቃድ አብስሎ መብላት፣ ከተማሪ ኳኳታ ገለል ብሎ መኖር፣ በፍቅር እፍ ማለት፣ የማይገፋውን የዩኒቨርስቲ ሕይወት መርሳት፣ መተሳሰብ፣ መረጋጋት…እነዚህ ሁሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳር ትሩፋቶች ናቸው፡፡

በአነስተኛና ጥቃቅን ትዳሮች የወር ወጪ እንጂ የቀን ወጪ ብሎ ነገር የለም፡፡ ወንዱም ጠዋት ጠዋት ሲወጣ ለሚስት የአስቤዛ ወጪ የመመደብ ግዴታ የለበትም። የአንደኛው ደሞዝ ሲመጣ የቤት ኪራይ ይከፈላል፡፡ በአንደኛው ደግሞ የወር ቀለብ ይሸመታል፡፡ የተረፈውን አንድ ቦታ አስቀምጠው መዘዝ እያረጉ መውሰድ ነው ።

የፍሰሀው ዘመን አልፎ ድህነት ሲመጣና ካዝናቸው ሲራገፍ ‹‹ባል›› ሆዬ ከየትም ከየትም ብሎ ገንዘብ የማምጣት ሀላፊነት ጫንቃው ላይ ይወድቃል። ችግሩ ባስ ካለም ባቅራቢያቸው ካለ ሱቅ ዱቤ ከመጠየቅ ጀምሮ በቤቱ ውስጥ አሉ የተባሉ ንብረቶችን እንደ ስልክና ላፕቶፕ ያሉትን አሲዞ አራጣ ብድር እስከመበደር ድረስ መስዋእትነት የመክፈል ግዴታ አለበት።

የትዳር ተጣማሪዎች ጓደኞቻቸውን ቤታቸው አምጥተው ማሳደር ቢፈልጉ ወንዱም ሴቷን፣ ሴቷም ወንዱን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።አብዛኛውን ጊዜ ወደባለትዳሮች እልፍኝ የሚያዘወትሩት የሴቷ ጓደኞች ናቸው፡፡ ይሄን ጊዜ ወንድየው ቤት ካለ ቶሎ ብሎ ሰላምታ አቅርቦ በሴቶች ሳይከበብ ውልቅ ይላል።

ትዳር በተለይ ለዩኒቨርስቲ ወንድ የሚሰጠው አንድ ዳጎስ ያለ ጥቅም አለ ከተባለ እግሩን እንዲታጠብ የምታስገድደው ደግ ሚስት  ማግኘት ነው፡፡ ካልሲዎቹን አጣጥባ የምታሰጣም አፍቃሪ ሚስት አለች፡፡ እንዲህ አይነቷን ሚስት የታደለ አቶ ‹‹ባል›› ጫማውን ማውለቅ ባሻው ጊዜ ሁሉ ሳይሳቀቅ ማውለቅ ይችላል።

ጥቃቅን ትዳር ለሴቷ የሚሰጠው ፋይዳ ቅናት፣ ሽኩቻና ዉድድር ከሚበዛበት አስጨናቂ የዶርም ሕይወት ወጥታ ከምትወደው ሰው ጋር በፍቅር መኖር መቻሏ ነው፡፡ “አብርሽዬን አቅፎ ከመኖር በላይ ምን ቀሽት ነገር አለ አቦ!!” ትላለች ፌቨን ስለ ትዳሯ ስትደሰኩር ። 

የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች  በተጣማሪዎች ዘንድ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ እንጂ እንደ መጀመሪያ ትዳር አይታዩም፡፡ ፌቨንም ብትሆን “ይሄ እኮ በቃ ዝም ብሎ ፈታ ለማለት ያህል ነው እንጂ ስልሽ….በቃ አለ አይደል...የምር ትዳር ትዳር አይደለም” ትላለች። አይበለውና ከአሁኑ ተጣማሪዋ ጋር ቢለያዩና ወደፊት ከሌላ ሰው ጋር ትዳር ብትመሰርት ‹‹ዩኒቨርስቲ አብሬው የምኖር ቦይፍሬንድ ነበረኝ›› ለማለት የምትደፍር አትመስልም።  



 የጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮች የመረዳዳት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ በትምህርት ትንሽ ሻል ያለው ለሌላው እገዛ ያደርጋል፤ ዋቢ መጻሕፍትን ያፈላልጋል፣ በኮምፒውተር ያስተይባል፣ ሌሊት ይቀሰቅሳል፣ ያስተዳድራል፣ ቡና ያፈላል ወይም ያስፈላል ወ.ዘ.ተ። ነገር ግን የትምህርት ሰዓት አልቆ የፈተና ሰዓት እየተቃረበ ሲመጣ በባለትዳሮች መካከል ኩርፊያና ንትርክ ይሰፍናል፡፡ ፍቅር ጥጓን ይዛ ኩምሽሽ  ብላ ትቀመጣለች። የፈተናው ቴንሽን ከአቅም በላይ ስለሚሆን ውሃ ቀጠነ ብለው መፎካከርና መበሻሸቅ ይጀምራሉ፡፡ የፉክክር ስሜት አይሎ እንኳን ሠርቶ መብላት በራቸውንም ሳይዘጉ ማደር ይከተላል።

ፈተናው ሲያልቅ ግን ነገሮች ቀስ በቀስ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ ፍቅር ከተኮራመተችበት ትወጣና በኩራት ስሜት እዛች ጠባብ ቤት ውስጥ አክሮባት መስራት ትጀምራለች። የፈተናውን ማለቅ ተከትሎ የመለያየት ስጋትና ጭንቀት ቦታውን ይረከባሉ፡፡

ሴሜስተሩ ያልቅና የመለያየትን ፅዋ መጎንጨት ግድ ይሆናል፡፡ እቃዎቻቸውን በፌስታል ሸፋፍነው፣ ፍራሻቸውን ጠቅልለው (ለነገሩ አጣጥፈው ቢባል ይቀላል) የማይኖሩበትን የሦስት ወር ቤት ኪራይ ከፍለው ወደየቤተሰቦቻቸው ይመለሳሉ። የባለትዳሮቹን ፍቅር ማለቅ ወይም አለማለቅ ተከትሎ ይህ እረፍት ለአንዳንዶቹ እረፍት ለአንዳንዶቹ ደግሞ ፍቺም ጭምር ነው።
ለፌቨንና አብርሀም እነዚህ ሁለት ወራት  የእፎይታ ጊዜያት አይደሉም፤ የናፍቆት አንጂ። የተለያየ ቦታ ስለሚኖሩ ሁለት ወሯ ሁለት ዓመት ትሆንባቸዋለች፡፡ ብዙ ሰዓት ስልክ በማውራት አብሮነት ስሜት ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህ አልበቃ ሲል ግን ትራስ አቅፎ ማልቀስ የፌቨን መጨረሻው ይሆናል።

እረፍቱ ሲያልቅ ፌቨን ወደ ግቢ ለመመለስ በጣም ከመቸኮሏ የተነሳ ለመሄድ ገና አስራ አምስት ቀን ሲቀራት ነው መዘገጃጀት የምትጀምረው፡፡ ልክ እንደ በሶና ዳቦ ቆሎ ሁሉ የሽሮና በርበሬው ዝግጅትም ቀላል የሚባል አይደለም። ቆይ ግን ይህን ሁሉ ሽሮና በርበሬ ምን ልታደርጊው ነው ስትባል “እዛ ከእህቷ ጋር ቤት ተከራይታ የምትኖር ጓደኛ ስላለችኝ እሷ ቤት እየሠራን እንበላለን ” የሚል መልስ ትሰጣለች፡፡ ምክንያቷ ያልተዋጠላቸው እናት “ቆይ ዩንቨርስቲው አያበላቹም እንዴ? ነው ወይስ የባልትና ሱቅ ከፍተሻል” እያሉ እንደሚቀልዱባት ትናገራለች።


ጥቃቅንና አነስተኛ ትዳሮችን በጣም ለየት የሚያደርጋቸው እንደ ሆሊዉድ የኮንትራት ትዳር የመመስረቻም ሆነ የመፍረሻ ጊዜያቸው የተቆረጠ መሆኑ ነው። ብዙዎቹ ተማሪዎች ትዳር የሚመሰርቱት ከወላጆቻቸው እውቅና ውጪ ስለሆነ የምርቃታቸው ቀን የፍቺያቸው ቀን የሚያሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።


ላጤ ተማሪዎች በትልቁ አዳራሽ ውስጥ ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ!›› ሲዘምሩ፣በደስታ ምድር ስትጠባቸው፣ በእፎይታ ስሜት ሲፍለቀለቁ፣ ጥቃቅን ባለትዳሮች በሀዘንና በፍርሀት መንታ መንታውን ያነቡታል። ፌቨን እንደዚህ ቀን የምትፈራው ቀን የላትም፡፡ የምረቃ ቀን የ‹‹እያነቡ እስክስታ ቀን›› ነው፣ ለፌቨን፡፡